2. ግርማ ገዛኽኝ - አልቀረቡም ለሁሉም ጠበቃ ወንድወሰን
3. ባዩ ጌታነህ ከማረ/ቤት - ቀረበ ተ/ማርያም - ቀረቡ
4. በለጠ አስፋ ከማረ/ቤት - ቀረበ
ተጠሪ፡- ፌዴራል አቃቤ ሕግ
መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሠጥተናል፡፡
በዚህ መዝገብ የቀረበው ጉዳይ የወንጀል ሲሆን ክርክሩ የተጀመረውም
በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ነው፡፡ በዚህ ፍ/ቤት የአሁኑ ተጠሪ በአሁኑ አመልካቾች ላይ የመሠረተው የወንጀል ክስ በሁለት ምድብ የተከፈለ
ሲሆን 1ኛው ክስ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወ/ህ/አንቀጽ
32(1(ሀ)(ለ))እና 539(1ሀ) ስር የተመለከተውን በመተላለፍ አመልካቾች በሙሉ ሐሳባቸውና አድራጎታቸው በወንጀሉ
ስራና በሚሰጠው ዉጤት ሙሉ ተካፋይ በመሆን ተበዳዮች ጌታነህ ወ/ማሪያም እና ደስታ ወ/ማሪያም የተባሉት በጥቅምት ወር 1985 ዓ/ም
በኢ.ሕ.አ.ዲ.ግ ታጋዮች 1ኛ/ ጌታነህ ወ/የስ ፣ 2ኛ/ መኮንን ጌታነህ ፣ 3ኛ/ በቀለች ወ/አረጋይ የተባሉ ቤተሰቦቻችንን አስገድለውብናል
በሚል ቂም በቀል ተነሳስተው ቤት ንብረታቸውን በእሳት አውድመው ከአገር እንዲሰደዱ ካደረጓቸው በኋላ እንደገና በፍርድ ቤት ከሰዋቸው
በነፃ ሲሰናበቱ 1ኛዋ አመልካች በተሰጠው የፍርድ ውሳኔ የበቀል ጥማቷ ባለመርካት ከአስር አመት በላይ
ተበዳዮቹ የሚኖሩበትን ቦታ ለማወቅ በግብረአበሮቿ አማካኝነት ስትከታተል ቆይታ በ2ኛው አመልካች አማካኝነት ቤታቸውን ካገኘች በኋላ
በተጨማሪም የተበዳይን ወንድሞች ቤት ጭምር ራሷ ፈልጋ በማግኘት ከቤታቸው ድረስ እየሄደች ስታጠና ቆይታ የወንጀሉን ሥራ መሪ ተዋናይ
በመሆን 3ኛ እና 4ኛ አመልካቾችን ከደብረ ብርሃን ፣ 2ኛ አመልካችን ከአዲስ አበባ በማሰባሰብ የአከባቢው ሰው በስራ የሚሰማራበትንና ጭር የሚልበትን አመቺ ጊዜ
አጥንተው ሰኔ 25 ቀን 1999 ዓ/ም ከጠዋቱ ከ4፡00 እስከ 6፡00 ባለው ጊዜ ውስጥ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በየካ ክፍለ
ከተማ ቀበሌ 07 ክልል ወደሚገኘው የሟቾች መኖሪያ ቤት በመሄድ ዘመድ ነን ብለው ሕፃናቱን በር ካስከፈቱ በኋላ ጨካኝታቸውንና አደገኛነታቸውን
እንዲሁም ነውረኝነታቸውን በሚገልፅ አስቃቂ ሁኔታ፡- 1ኛ/ ህፃን ፍቅረተ በቀለ እድሜዋ 12 አመት የሆነችውን ፣ 2ኛ/ ሕፃን ሐና
በቀለ እድሜዋ 8 አመት የሆነችውንና 3ኛ ሕፃን ነጻነት በቀለ እድሜዋ
1 አመት ከ8 ወር የሆነችውን ከሟች ሕፃን ፍቅረተ በቀለ ጀርባ እንደታዘለች ሶስቱንም ሕጻናት በዱላ ጭንቅላታቸውን እና
መላ ሰውነታቸውን እየተፈራረቁ ቀጥቅጠው በግፍ ገድለዋል የሚል ሲሆን 2ኛው ክስ ደግሞ ሁሉም አመልካቾች በ1996 ዓ/ም በወጣው
የወንጀል ሕግ አንቀጽ 669(3(ለ)) ስር የተመለከተውን በመተላለፍ አመልካቾች ሕገ ወጥ ብልፅግና ለራሳቸው ለማግኘት በማሰብ በቡድን
ተደራጅተው በ1ኛው ክስ ላይ በተገለጸው ጊዜና ስፍራ በክሱ ላይ የተመለከተውን የግፍ ግድያ ወንጀል ከፈጸሙ በሁዋላ ንብረትነቱ የአቶ
በቀለ ወ/ማሪያም የሆኑ፡- ባለ 14 ኢንች ኤልጂ (LG) ቴሌቭዥን
፣ ሶስት ጋቢዎች ፣ አንድ ሰማያዊ ሸራ ላስቲክ እና አንድ አሮጌ የማዳበሪያ ከረጢት ሰርቀው በመውሰዳቸው ከባድ የስርቆት ወንጀል
ፈጽመዋል የሚል ነው፡፡ አመልካቾች ክሱን ክደው በመከራከራቸውም ዐቃቤ ሕግ አሉኝ ያላቸውን የሰውና የሰነድ ማስዎችን አቅርቦ አሰምቷል፡፡ከዚህም
በኋላ የአመልካቾች የመከላከል መብት ተጠብቆላቸው የመካለከያ ማስረጃዎችን አቅርበው አሰምተዋል፡፡ ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም አመልካቾች የዐቃቤ ሕግ ማስረጃዎችን ያላስተባበሉ መሆኑን ዘርዝሮ የመከላከያ ማስረጃዎቻቸውን ቃል
ውድቅ ያደረገ ሲሆን አመልካቾችን በዐቃቤ ሕግ በኩል ተጠቅሰው በቀረቡባቸው ድንጋጌዎች ስር ጥፋተኛ በማድረግ የጥፋተኝነት ውሳኔ
ሰጥቷል፡፡ በቅጣት ረገድም የአሁኗ 1ኛ አመልካችን (መስታወት ጌታነህን) በሞት ፣ ሌሎች አመልካቾችን ደግሞ በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ሲል በድምፅ ብልጫ ወስኗል፡፡ አመልካቾች በስር ፍርድ ቤት
በተሰጠው የጥፋተኝነም ሆነ የቅጣት ውሳኔ ይግባኛቸው ለፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቢያቀርቡም ተቀባይነት አላገኙም፡፡ በሌላ በኩል
ዐቃቤ ሕግ ከ2ኛ እስከ 4ኛ ተራ በተጠቀሱት አመልካቾች ላይ የተሰጠውን የቅጣት ውሳኔ ሕጋዊነት የለውም ፤ ያነሰ ነው በሚል ምክንያት
ይግባኙን ለፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቅርቦ ግራ ቀኙ ከተከራከሩ በሁዋላ የአመልካቾችን የድርጊት አፈጻፀም ከሕጉ ጋር በመመርምር
አመልካቾች ሊቀጡ የሚገባው በሞት ነው በማለት የስር ፍርድ ቤትን የቅጣት ውሳኔ አሻሽሎ ወስኗል፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም
በጥፋተኝነት እና በቅጣት ውሳኔው ላይ ነው፡፡
የአመልካቾች የሰበር
አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም ድርጊቱን አመልካቾች ስለመፈጸማቸው በወንጀል ሕግ የማስረጃ ምዘና መርህ ባልተረጋገጠበት ሁኔታና በፖሊስና
በፍርድ ቤት አመልካቾች ሰጡ የተባሉት የእምነት ቃል በኃይል የተገኘ ሁኖ እያለ የወንጀል ድርጊቱን ፈጽማችኋል ተብሎ የመከላከያ
ማስረጃዎችን እንድናቀርብ ብይን መሰጠቱ ያላግባብ ከመሆኑም በላይ የመከላከያ ማስረጃዎች ቃል ውድቅ የተደረገው ያላግባብ ነው ፣
የቅጣቱ ውሳኔም ሕጉን የተከተለ ሳይሆን የተጋነነ ነው በማለት ውሳኔው እንዲታረም ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚሳይ ነው፡፡ አቤቱታው
ተመርምሮም አመልካቾች እያንዳንዳቸው በሞት እንዲቀጡ ተብሎ የተወሰነው የቅጣት ውሳኔ ተገቢ መሆን ያለመሆኑን ለመመርመር ሲባል ለሰበር
ችሎቱ እንዲቀርብ የተደረገ ሲሆን የግራ ቀኙ የቃል ክርክር ታህሳስ 07 ቀን 2002 ዓ/ም በዋለው ችሎት ተሰምቷል፡፡
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን
ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር የሠበር አቤቱታው ከቀረበበት ውሣኔ እና አግባብነት ካላቸው የህግ ድንጋጌዎች አኳያ በሚከተለው
መልኩ መርምሮታል፡፡ እንደመረመረውም የዚህን ችሎት ምላሽ የሚያስፈልገው አቢይ ነጥብ የፌዴራሉ ጠቅላይ
ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የቅጣት ውሳኔ
መሠረታዊ የሆነ የህግ ስህተት አለበት ወይስ የለበትም? የሚለው ሁኖ አግኝቶታል፡፡
ከክርክሩ ሂደት
መገንዘብ የተቻለው አመልካቾች ሶስቱን ህፃናት ለሕልፈተ- ሕይወት ዳርገዋል ፣ ከባድ የስርቆት ወንጀል ፈጽመዋል ተብሎ በግፍ የሰው ግድያና በከባድ የስርቆት ወንጀል ጥፋተኛ የተባሉበት በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር
27(2) ለፖሊስ ፣ በወ/መ//ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 35 ደግሞ ለፍርድ ቤት ሰጡ በተባሉት የእምነት ቃል ፣ የድርጊቱን አፈጻጸም መርተው
ሲያሳዩ በተነሱት ገላጭ ማስረጃና በጠንካራ አካባቢ የሰው ምስክሮች ቃል ስለመሆኑ የበታች ፍርድ ቤቶች ውሳኔ በግልፅ ተጠቅሷል፡፡
የአመልካቾች የመከላከያ ምስክሮች ቃል ውድቅ የተደረገውም አመልካቾች የእምነት ቃሉን የሠጡት በኃይል ስለመሆኑ ለማስረዳት እምነት
ሊጣልበት የሚችል አይደለም በሚል ምክንያት ነው፡፡ እንግዲህ የበታች ፍርድ ቤቶች አመልካቾች ድርጊቱን ፈፀሙ በማለት ድምዳሜ ላይ
የደረሱት አመልካቾች እያንዳንዳቸው በድርጊቱ አፈጻጸም ላይ የነበራቸውን ቀጥተኛ ተሳትፎ በሚገባ አቃቤ ሕግ አስረድቷል ፣ በመከላከያ ማስረጃዎቻቸውም አልተደገፉም በሚል ነው፡፡የአመልካቾች
ጠበቃ ከሚከራከሩባቸው ነጥቦች ውስጥ የአመልካቾችን የድርጊት ፈጻሚነት በተገቢው መንገድ አቃቤ ሕግ በማስረጃ ያለማስደገፉንና የአቃቤ
ሕግ ማስረጃዎችን አመልካቾች በመከላከያ ምስክሮች የማስተባበላቸው ሁኔታን የሚመለከቱ ነጥቦች የሚገኙ ሲሆን የበታች ፍርድ ቤቶች
ተገቢውን የማስረጃ ምዘና መርህ ተከትለው አመልካቾችን ጥፋተኛ ያደረጉ ስለመሆኑ የክርክሩ ሂደት የሚያሳየን ሁኖ አግኝተነዋል፡፡
በመሆኑም ከዚሁ የበታች ፍርድ ቤቶች ውሳኔ መገንዘብ የሚቻለው አመልካቾች ጥፋተኛ የተባሉት በጉዳዩ ላይ የቀረቡት ማስረጃዎች ተመዝነው
መሆኑን ነው፡፡ እንደሚታወቀው ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት አንድ የመጨረሻ ፍርድ ያገኘን ጉዳይ ማረም የሚችለው በውሳኔ ላይ መሰረታዊ
የሆነ የሕግ ስህተት መኖሩ ሲረጋገጥ ስለመለሆኑ በኢ.ፌ.ዲ.ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት አንቀጽ 80(3(ሀ)) እና አዋጅ ቁጥር
25/1988 አንቀጽ 10 ተመልክቷል፡፡ ከእነዚህ ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ መገንዘብ የሚቻለው ደግሞ ይህ ሰበር ችሎት ፍሬ ነገርን
የማጣራት ወይም ማስረጃን የመመዘን ስልጣን የሌለው መሆኑን ነው፡፡ በተያዘው ጉዳይም የአመልካቾች ጠበቃ አጥብቀው የሚከራከሩባቸው
ነጥቦች የመሰረታዊ ሕግ ስህተት መመዘኛን መሰረት ያደረጉ ሳይሆን የፍሬ ነገርንና የማስረጃ ምዘናን መሰረት ያደረጉ በመሆናቸው በዚህ
ችሎት ሊታዩ የሚችሉ ሁነው አላገኘናቸውም፡፡በመሆኑም አመልካቾች የእምነት ቃላቸው በመገደድ የተገኘ ስለመሆኑ ማረጋገጥ ባልቻሉበት
ሁኔታና በራሳቸው ምሪት ወንጀሉ የተሰራበትን ቦታና የአፈጻጸሙን ሁኔታ ስለማሳየታቸው በሰነድ ማስረጃ ተረጋግጦ ባለበት የክርክር
ሂደት እንዲሁም ወንጀሉ በአመልካቾች ስለመፈጸሙ ደግሞ በበርካታ ጠንካራ የአካባቢ ማስረጃዎች ተደግፎ በቀረበበት መንገድ አመልካቾች
የአቃቤ ሕግ ማስረጃ በሕጉ መመዘኛ የሚያሟላ አይደለም በማለት የሚያቀርቡት ክርክር የሕግ መሰረት ያለው ሁኖ አልተገኘም፡፡ አመልካቾች
ለድርጊቱ ኃላፊነት አለባቸው ተብሎ የተወሰነው ወንጀሉ መሰራቱ ወይም መፈጸሙና ተሰራ ወይም ተፈጸመ የተባለው ወንጀል ደግሞ በአመልካቾች
መፈጸሙ በማያጠራጥር ሁኔታ ፍሬ ነገርን የማጣራትና ማስረጃን የመመዘን ስልጣን ያላቸው ፍርድ ቤቶች ያረጋገጡት ጉዳይ በመሆኑና ይህም
በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 23 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ የሚያሟላ በመሆኑ በዚህ ረገድ የቀረበውን ክርክር የምንቀበለው ሁኖ አላገኘነውም፡፡
ወደዋናው ጭብጥ ስንመለስም የአመልካቾች
መሠረታዊ ክርክር የበታች ፍርድ ቤቶች ያስተላለፉት የሞት ቅጣት የቅጣት አወሣሠኑን በተመለከተ የወንጀል ህጉ ያስቀመጣቸውን መርሆዎች
ያላገናዘበ ነው የሚል ነው፡፡ እኛም ይህንኑ ቅሬታ ከህጉ ጋር አገናዝበን ተመልክተናል፡፡
በመሠረቱ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ የወንጀል
ህግ የአገሪቱን የወንጀል ህግ ግብ በአዋጅ ቁጥር 414/1996 አንቀጽ 1 ስር ሲደነግግ “የወንጀል ህግ ግብ ወንጀል እንዳይፈፀም
መከላከል ሲሆን ይህንን የሚያደርገው ስለወንጀሎችና ስለቅጣታቸው በቅድሚያ ማስጠንቀቂያ በመስጠት፣ ማስጠንቀቂያነቱ በቂ ባልሆነበት
ጊዜ ወንጀል አድራጊዎቹ ተቀጥተው ሌላ ወንጀል ከመፈፀም እንዲቆጠቡና ለሌሎች ማስተማሪያ እንዲሆኑ ወይም እንዲታረሙ በማድረግ ወይም
ተጨማሪ ወንጀሎች እንዳይፈፀሙ እርምጃዎች እንዲወሰዱባቸው በማድረግ ነው” በማለት ያስቀምጣል፡፡ ህጉ በአንቀጽ 87 ላይ ቅጣቶችና
የጥንቃቄ እርምጃዎች ህጉ ሊደርስበት ያሠበውን ዓላማ ለማረጋገጥ በሚቻልበት ሁኔታ በህጉ መንፈስ መሠረት መፈፀም እንዳለባቸው በመርህ
ደረጃ ይደነግጋል፡፡ ይኸው አንቀጽ ቅጣቶችና የጥንቃቄ እርምጃዎቹ ምን ጊዜም ሠብዓዊ ክብርን በሚጠብቅ መንገድ መፈፀም እንደሚኖርባቸው
ያስገነዝባል፡፡ የወንጀል ህጉ አንቀጽ 88 ሲታይም የቅጣቶች እና የጥንቃቄ እርምጃዎች አወሣሠንን በተመለከተ ዘርዘር ያሉ ንዑስ
ድንጋጌዎችን አካቶ ይዟል፡፡ በዚህ አንቀጽ ስር ያሉ ንዑስ አንቀጾች የሚያሣዩት ፍርድ ቤቱ ቅጣቶችንና የጥንቃቄ እርምጃዎችን የሚወሰነው
የወንጀል ህጉን ጠቅላላ ክፍል ድንጋጌዎችን እንዲሁም ስለወንጀሎችና ስለቅጣታቸው የሚደነግጉትን የልዩ ክፍሉ ድንጋጌዎች መሠረት በማድረግ
መሆኑን ፣ ቅጣት ሊወሰን የሚገባው የወንጀል አድራጊውን ግላዊ የአደገኛነት መጠን ያለፈ የህይወት ታሪኩን ወንጀል ለማድረግ ያነሣሡትን
ምክንያቶችና የአሣቡን ዓላማ የግል ኑሮውን ሁኔታ፣ የትምህርቱን ደረጃ ፣ እንዲሁም የወንጀሉን ከባድነትና የአፈፃፀሙን ሁኔታዎች
በማመዛዘን መሆኑን፣ የወንጀል ህግ ልዩ ክፍል ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆኖ ፍርድ ቤቱ እጅግ ቀላል ከሆነው ቅጣት አንስቶ እስከ
ከባዱ ድረስ ያለውን በጥንቃቄ በመመርመር ለእያንዳንዱ ጉዳይ ተገቢ የሆነውን ቅጣት እንደሚወስንና የቅጣት አወሣሰን ትክክለኛነትና
አንድ ወጥነት ለማረጋገጥ የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት የቅጣት አወሣሠን መመሪያ (Manual) እንደሚወጣ የሚያስገነዝቡን ናቸው፡፡
ከላይ ከተመለከቱት ድንጋጌዎች የምንረዳው አቢይ ነጥብ ቅጣቶች
መወሠን ያለባቸው የህጉን መንፈስ በመከተል ዓላማዎችንና ግቦቹንም ተፈፃሚ በማድረግ ሀሣብ መሆኑን ነው፡፡ የህጉን መንፈስ ከመተግበር
አኳያ ወንጀለኛውን ማዕከል የማድረግ ፅንሰ ሀሣብ አጽንኦት የተሠጠው ጉዳይ ነው፡፡ ዳኞች በፅንሰ ሀሣቡ መሠረት የተሠጣቸውን አመዛዝኖ
የመወሰን ስልጣን (Discretion) በስራ ላይ ሲያውሉ ሠብአዊ ክብርን ከማስጠበቅ ዓላማ ጋር መሆን ያለበት ከመሆኑም በላይ ህግ
አውጪው በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 87/1/ ስር የተመለከቱትን መሠረት በማድረግ ዳኞች የቅጣት ውሣኔ በምን መንገድ መወሠን እንደሚገባቸው
በአንቀጽ 88 ስር አስቀምጧል፡፡ በወንጀል ህጉ የተመለከቱትን ድንጋጌዎች ስንመለከትም ዳኞች ከተሠጣቸው የቅጣት ክልል ሣይወጡ የአጥፊውን
ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ቅጣት እንዲወስኑ ህጉ ስልጣን የሠጣቸው መሆኑ ነው፡፡ ዳኞች አጥፊውን በተመለከተ ከግምት ውስጥ
ሊያስገቧቸው የሚገባቸው በርካታ የአጥፊ ፡ ሁኔታዎች ቢኖሩም የቅጣት አወሣሠናቸው መሠረት የወንጀል አድራጊውን ግላዊ የአደገኛነት
መጠን /degree of individual guilt/ ስለመሆኑ የአንቀጽ 88/2/ ድንጋጌ ይዘትና አቀራረፅ ያስረዳል፡፡ አንቀጽ
88(2) በመጀመሪያ ደረጃ የወንጀል አድራጊውን የአደገኛነት መጠን መሠረት በማድረግ ዳኞች ቅጣት እንዲወስኑ ማድረጉና ይህንን ሲወስኑም
በድንጋጌው የተመለከቱትን የወንጀሉን አፈፃፀም የአጥፊውን ያለፈ የህይወት ታሪኩንና የኑሮ ሁኔታ ከግምት በማስገባት በማመዛዘን ለወንጀሉና
ለወንጀለኛው የሚገባውን የቅጣት መጠን እንዲወስኑ መደንገጉ የቅጣት ውሣኔዎችንና እርምጃዎችን እየተራራቁ እንዳይወሠኑ የማድረግ ጠቀሜታ
ይኖረዋል ተብሎ ከመታሠቡም በተጨማሪ ችግሩ የሚቀረፍበትና የሚቀነስበትን ሥርዓትም ህጉ ዘርግቷል፡፡ ዳኞች ቅጣት ሲወስኑ በህጉ አንቀጽ
88(2) ለአጥፊው ተገቢ ነው ያሉትን ቅጣት ከወሠኑ በኋላ በህጉ የተመለከቱትን የማቅለያና የማክበጃ ድንጋጌዎችን መሠረት በማድረግ
ቅጣቱን ከፍ ወይም ዝቅ ለማድረግ የሚችሉ ስለመሆኑ ህጉ ያሣያል፡፡
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የወንጀል ህግ በአንቀጽ 84(1) ከፊደል
(ሀ) እስከ ፊደል (ሠ) ድረስ ጠቅላላ የቅጣት ማክበጃ ምክንያቶችን ካስቀመጠ በኋላ በአንቀጹ ንዑስ ቁጥር ሁለት ስር በንዑስ ቁጥር
አንድ ስር የተመለከቱት የማክበጃ ሁኔታዎች በህጉ ልዩ ክፍል ተካተው ሲገኙ በድጋሚ በማክበጃነት ዳኞች እንዳይጠቀሙ ያሣስባል፡፡
ስለሆነም የህጉ አንቀጽ 84 ደግሞ የቅጣት ማክበጃ ምክንያቶችን የዘረዘረ ሲሆን ዳኞች የህጉን አንቀጽ 183 ባገናዘበ መልኩ ቅጣት
የሚያከብዱባቸውን ሁኔታዎች ያሣያል፡፡ ዳኞች ቅጣትን የሚቀንሱትም ሆነ የሚያከብዱት ተገቢ ሁኖ ሲገኝ ስለመሆኑ የአንቀጽ 179 እና
183 ድንጋጌዎች ያሣያሉ፡፡ አንቀጽ 179 የቅነሣውን ገደብ የሚያሣይ ሲሆን ከዚህ መደበኛ ቅነሣ በተጨማሪ ልዩ ቅነሣ ለማድረግ
እንደሚቻልም ህጉ በአንቀጽ 180 ስር አስቀምጧል፡፡ በህጉ አንቀጽ 86 ቅጣትን በማቅለልም ሆነ በማክበድ ረገድ ከህጉ አንቀጽ
179፣182 እና ውጪ የሆኑ ምክንያቶች ሲያጋጥማቸው ዳኞች ምክንያታቸውን በመግለፅ ቅጣቶችን ለመቀነስ ወይም ለማክበድ እንደሚችሉ
ተደንግጓል፡፡ ግንቦት 09 ቀን 2002 ዓ/ም ጀምሮ ተግባራዊ በሆነው
የቅጣት መመሪያ ውስጥ የተቀመጠው የቅጣት አወሳሰን ሥርዓት እንደተጠበቀ ሁኖ ከላይ ስለቅጣት አወሣሰን በህጉ የተመለከቱት
ድንጋጌዎች ሲታዩ የሚያስገነዝቡን ዓቢይ ነጥብ ቅጣቶችን በመጣልና እርምጃዎችን በመውሠድ ረገድ ዳኞች አመዛዝነው የመወሠን ከፍተኛ ስልጣን ያላቸው መሆኑን ነው፡፡
ወደተያዘው ጉዳይ ስንመለስም አመልካቾች ጥፋተኛ የተባሉት
ግዙፍነት ባላቸው ተደራራቢ ወንጀሎች ሲሆን የግድያ ወንጀሉ በወንጀል
ሕጉ አንቀፅ 32(1(ሀ)(ለ)) እና 539(1ሀ)) ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ በቂም ፣ ጨካኝነት ፣ ነውረኝነት ፣ አሰቃቂና
አደገኛነትን በሚያሳይ ሁኔታ ምንም የማያውቁ ጨቅላ ሕጻናትን በግፍ ገድለዋል ተብሎ ነው፡፡ በዚህ ድንጋጌ ጥፋተኛ የተባለ አጥፊ
ሊቀጣ የሚገባው እድሜ ልኩን በጽኑ እስራት ወይም በሞት ነው፡፡ ከላይ እንደተመለከተው ፍርድ ቤት ቅጣት ሲወስን ሊከተላቸው የሚገባቸው
የቅጣት አወሳሰን መርሆዎች በሕጉ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የወንጀል ይግባኝ ሰሚ ችሎት በአመልካቾች ላይ
ያስተላለፈው የሞት ቅጣት ስለመሆኑም ከላይ ገልፀናል፡፡
በመሰረቱ ማንኛውም ሰው በሕይወት የመኖር መብት እንዳለውና
በሕግ በተደነገገው ከባድ የወንጀል ቅጣት ካልሆነ በስተቀር ሕይወቱን ሊያጣ እንደማይገባ የኢ.ፌ.ዲ.ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት በአንቀፅ
15 ስር በኃይለ ቃል የደነገገው ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም በሕጉ አግባብ
ከባድ ወንጀል መፈጸሙ በተረጋገጠበት ሰው ላይ የሞት ቅጣት ማስተላለፍ የሚፈቀድ መሆኑን ሕገ መንግስቱ አስቀምጧል፡፡ በሌላ በኩል
የሞት ቅጣት ሊተላለፍ የሚገባበትን አግባብ የወንጀል ሕጉ በአንቀጽ 117 ስር ድንግጎ እናገኛለን፡፡ በዚህ አንቀፅ ንዑስ ቁጥር
አንድ ድንጋጌ መሰረት የሞት ቅጣት የሚወሰነው ወንጀሉ ፍጻሜ ያገኘ ሁኖ እጅግ በጣም ከባድ በመሆኑና ወንጀለኛውም በተለይ አደገኛ
በመሆኑ ለወንጀሉ ቅጣት እንዲሆን በሕጉ በግልጽ ተደንግጎ በተገኘ ጊዜ እንዲሁም ለወንጀለኛው ቅጣትን የሚያቀልለት ምክንያት በታጣ
ጊዜ እድሜው ቢያንስ አስራ ስምንት አመት የሞላው ሁኖ ሲገኝ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ አመልካቾች ጥፋተኛ የተባሉበት ድንጋጌ እድሜ ልኩን
በፅኑ እስራት ወይም በሞት የሚያስቀጣ ነው፡፡ የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሞት ቅጣቱን ለመወሰን የቻለውም ድርጊቱን ለመፈጸም
ያነሳሳቸውን ምክንያት ፣ ድርጊቱን ለመፈጸም ለረዥም አመታት ሲደረግ የነበረውን ቅድመ ዝግጅትና እና ድርጊቱ የተፈጸመባቸው
ምንም የማያውቁና ከማንኛውም ሰው እንክብካቤ የሚሹ ሶስት ጨቅላ ህጻናት
ላይ መሆኑን እንዲሁም የአፈጻጸሙን ዘግናኝነትና አስቃቂነት ከአመልካቾች አደገኛ ባህርይና ቅጣቱ ለሌላው ማህበረሰብ ሊያስተላልፈው
ከሚችለው መልዕክት በመነሳት ከመሆኑም በላይ ለአመልካቾች በሕጋዊ ማቅለያነት ሊያዙ የሚችሉ ምክንያቶች የሌሉ መሆኑን በመረዳት መሆኑን
ከውሳኔው ይዘት ተገንዘበናል፡፡ በመሆኑም በዚህ ረገድ በፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተያዘው ምክንያትና የተደረሰው ድምዳሜ በቅጣት
አወሳሰን ጊዜ ግንዛቤ ውስጥ ሊገቡ የሚችሉ የቅጣት አወሳሰን መሰረታዊ መርሆዎችን ያልተከተለ ነው ለማለት የሚቻል ሁኖ አልተገኘም፡፡
ሲጠቃለልም በአመልካቾች ላይ የተጣለው የሞት ቅጣት የወንጀል
ሕጉን መሰረታዊ ግብና ዓላማ እንዲሁም የቅጣት አወሳሳን መርሆዎችን
ከድርጊቱ አፈጻፀም ጋር ያገናዘበ በመሆኑ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ነው ለማለት ስላልተቻለ ተከታዩን ውሣኔ ሰጥተናል፡፡
ው
ሳ ኔ
1.
በፌዴራሉ
ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በወ/መ/ቁ 45475 ሰኔ 26 ቀን 2001 ዓ.ም ፣ 45693 ሰኔ 26 ቀን 2001 ዓ/ም
እና በመ/ቁጥር 45640 ሰኔ 26 ቀን 2001 ዓ/ም የሰጣቸው ውሳኔዎች በወ/መ/ህ/ሥ/ሥ/ቁ 195(2)(ለ-2) መሠረት ጸንተዋል፡፡
2.
አመልካቾች
በሞት እንዲቀጡ ተብሎ መወሰኑ ባግባቡ ነው ብለናል፡፡ የሞት ቅጣቱ ተፈጸሚነት የሚኖረውም በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 117(2) መሰረት
በአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ከፀና በሁዋላ ይሆናል ብለናል፡፡
3.
በፌዴራል
ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የተሰጠው የሞት ቅጣት የፀና መሆኑን አውቆ ቅጣቱን ተከታትሎ እንዲያስፈጽም ለአዲስ አበባ
ማረ/ቤት ይፃፍ ብለናል፡፡
መዝገቡ ተዘግቷል፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡
የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት